በዞኑ የሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ባለፈ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም(ወልቂጤ) የጉራጌ ዞን ሴቶች ፌዴሬሽን የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም፣ በ100 ቀናት ዕቅድ ያተኮረ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የሴት አካል ጉዳተኞች ለብቻ ማደራጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር ተደርጓል ።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲሀ መህዲ እንዳሉት በዞኑ ሴቶች በሁሉም የልማት ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለዉን ስራ የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠልና በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት ይገባል።

በሩብ አመቱ የተከናወኑ አበረታች ተግባራት ይበልጥ ከማስቀጠል ባለፈ ጉድለቶችን በማረም ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዞኑ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖበታል ነው ያሉት።

አካልጉዳተኞች መደገፍና ማደራጀት ትልቅ የህሊና ስራ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ፈቲሃ በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር በዘርፉ የበለጠ መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሰብሳቢ ወይዘሮ ሊዲያ ሳኒ በበኩላቸው፥ ተቋሙ ሴቶች በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዲሞክራሲያዊ ግንባታ ስርዓት ሂደት ውስጥ በማሳተፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከመስራት ባለፈ ቋሚ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም በዞኑ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ በተለያዩ ወረዳዎች የውሀ አማራጮችን በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ ተድራጅተው እንዲሰሩ በማድረግ በተሰራው ስራ ውጤት ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

በተለይም በሴቶች ላይ የሚስተዋሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና አሉታዊ አመለካከቶች ለመቅረፍ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች መሰራቱን ጠቅሰው በቀጣይም መሰል የአመለካከት ውስንነቶችን ለማረም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በዞኑ አጠቃላይ የአባል አደረጃጀት 1 መቶ 76 ሺ በላይ ሲሆን በዚህም ውስጥ ከ 11 ሺ በላይ አካል ጉዳተኛ ሴቶች መሆናቸው ጠቅሰው፤ ከ8ሺህ በላይ የነጋዴ ሴቶች ማህበር እንደሚገኙበትም አብራርተዋል።

በቀጣይም የሴቶች የአመራርነት ብቃታቸውና ውሳኔ ሰጪነታቸው በማሳደግ ረገድ ሁሉም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊያደረግበት እንደሚገባም ወይዘሮ ሊዲያ አስገንዝበዋል።

የዞኑ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሮዛ አግዛ እንደገለጹት የዞኑ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ቀድሞ ከተቋቋሙት ማህበራት ልምድ በመውሰድ በርካታ ስራዎች መሰራቱን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የነጋዴ ሴቶች ማህበራት ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ በየዘርፉ ያሉ ውስነቶች ለመቀረፍ ይበልጥ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት የዞኑ ሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎች ይበልጥ ዉጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ አንስተዋል።

ቀጣይ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመቅረፍና የሴቶች አደረጃጀት በማጠናከር ሴቶች ወደ ፊት እንዲመጡ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ረገድ ይበልጥ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

በመጨረሻም የፌዴሬሽንና የማህበር ስራ አስፈጻሚ በአዲስ በመምረጥ አጽድቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *