ዞናችን በስፖርት ዘርፍ ያለው አቅምና ጸጋን በአግባቡ በመጠቀም ማህበረሰቡን ሊመጥን የሚችል ውጤት እንዲመጣ በትኩረት ይሰራል፦አቶ መብራቴ ወ/ማርያም

ጥቅምት 27/2019(ወልቂጤ)

የጉራጌ ዞን የስፖርት ምክር ቤት የ2018 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም እና የ2019 እቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ወ/ማርያም እንደገለጹት ስፖርት በአሁኑ ወቅት ከመዝናኛነት ባለፈ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ ለአብሮነትና ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ዘርፍ ነው።

የስፖርት ልማትን ለማጠናከርም መንግሥትን፣ ባለሀብቶችንና አርሶ አደሩን በማሳተፍ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማደራጀትና የውድድር ተሳትፎን ማሳደግ ያስፈልጋል።

በተለይም ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን በስፖርት እንቅስቃሴዎች በስፋት በማሳተፍ አካታችነትን ማረጋገጥና የስፖርት ገቢን በልዩ ትኩረት ማሳደግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዞኑ በርካታ ስፖርተኞችን፣ ዳኞችንና አሰልጣኞችን በማፍራት ለሀገር ባለውለታ መሆኑን ያነሱት አቶ መብራቴ፤ ይህንን አኩሪ ታሪክ በአሁኑ ትውልድ መድገም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ጉራጌ ዞን በስፖርት ዘርፍ ያለው አቅምና ጸጋን በአግባቡ በመጠቀም ማህበረሰቡን ሊመጥን የሚችል ውጤት እንዲመጣ በትኩረት ይሰራል ብለዋል አቶ መብራቴ።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ረሻድ የስፖርት ዘርፉ ለማጠናከር ሀብት አሰባሰብ ማሳደግ፣በሁሉም ስፖርቶች መሳተፍ፣ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት፣ኦዲት ማድረግ፣የስፖርት ምክር ቤት ጉባኤዎች በአግባቡ ማካሄድ ያስፈልጋል።

የወልቂጤ ስቴዲየም ደረጃው የጠበቀ ለማድረግ የዞኑ መንግስት እቅድ አቅዶ እየሰራ መሆኑ አመላክቷል።

አምና በቁርጠኝነት በተሰሩ ስራዎች በክልሉ የስፖርት ሻምፒዮና በአንደኝነት ማጠናቀቅ ተችሏል ያሉት አቶ ሙራድ በቀጣይም የዞኑ ማህበረሰብ የሚመጥን ውጤት ለማምጣት በአጽንኦት ይሰራል ብለዋል።

በ2019 ዓ.ም ደግሞ ከተለያዩ ምንጮች ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን በመጥቀስ የስፖርት ልማቱን በሀብትና በተሳትፎ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የመምሪያው ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደም ሽኩር በበኩላቸው የውስጥ ለውስጥ ስፖርት ውድድሮች በመካሄዳቸው፣በሁሉም ስፖርቶች ተሳታፊነት፣አካታችነትና ቅንጅጅ በመጠናከሩ የዞኑ ስፖርት እያደገ ይገኛል።

በታዳጊ ስፖርተኞች ላይ ለውጥ እንዲመጣ የዘቢደር አትሌቲክስ ክለብ እና በሌሎች የስፖርት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እየተሰራበት ነው ሲሉ አቶ አደም አስታውቀዋል።

በጉራጌ ዞን የስፖርት ልማትን ለማሳደግ የስፖርት ሀብትን በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ የህብረተሰቡን ተሳትፎና ስፖርት ምክር ቤቶችን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ አካላት ጉራጌ ዞን በስፖርት ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅምና ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም የስፖርቱን ልማት ማሳደግና ለዘርፉ ቀጣይነት ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሥነ ምግባር የታነጹ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ የማስ ስፖርት እንቅስቃሴዎችንና የውስጥ ለውስጥ ውድድሮችን ማጠናከር፣ የስፖርት ገቢን ማሳደግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አካታችነትና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል።

በመጨረሻም በ2018 ለስፖርቱ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተበርክቶላቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *