በዞኑ ለኢንደስትሪ ማዕከላት ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ መስመር መዘርጋቱ በዘርፉ ይስተዋል የነበረው የሀይል አቅርቦት እጥረትና መቆራረጥ በመቅረፍ ምርታማ እንዲሆኑ የላቀ ሚና ይጫወታል :- አቶ ደሳለኝ ገብሬ

ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም(ወልቂጤ) የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ ልማት መምሪያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ለኢንደስትሪ ማዕከል ብቻ የሚውል የመስመር ዝርጋታ ብሬከር በወልቂጤ ሰብ ስቴሽን ርክክብ አድርጓል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ገብሬ እንዳሉት የሀገሪቷ ብልጽግና ለማረጋገጥ በኢንደስትሪው ዘርፍ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ለዚህም በዞኑ የኢንደስትሪ ማዕከላት ላይ ይስተዋል የነበረው የሀይል አቅርቦት እጥረትና መቆራረጥ በመቅረፍ ምርታቸው በውጤታማነት ከማምረት ባለፈ ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ዞኑ እንዲገቡ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

የኢንደስትሪ ማዕከላት ራሱን አስችሎ የሀይል አቅርቦት እንዲያገኙ መደረጉ በዞኑ የሚስተዋለው የሀይል መቆራረጥ በመቀነስ ማህበረሰቡ የተሻለ የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ አበበ እድሉ የኢንደስትሪ ማዕከላት ከሌሎች መስመሮች አንድ በመሆኑ ኢንደስትሪዎቹ በሚፈለገው መልኩ ኤሌክትሪክ አግኝተው ስራቸው ለማሳለጥ ተግዳሮት ሆኖባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

የሃይል መስመር ዝርጋታው ፍብሪካዎችን ብቻ ታሳቢ ተደርጎ መዘርጋቱ ፋብሪካዎች 24 ሰዓት ስራ እንዲሰሩ በማድረግ ምርታማ እንዲሆኑ ያስችለዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም ቀደም ሲል ይከሰት የነበረውን የሃይል መቆራረጥ ችግር ይቀርፋል ብለዋል።

አክለውም ከዚህ ቀደም የወልቂጤ ከተማ የውሃ መስመር ምሶሶ አርጅቶ በመውደቁ ምክንያት የውሃ መስመር እንዲስተጓጎል ያደርግ እንደነበር አንስተው አሁን ላይ ይህ ወደ ተግባር ሲገባ በመብራት መቆራረጥ ምክንያት የሚስተዋለው የውሃ አቅርቦቱ ችግር እንደሚቀርፍም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በወረዳዎች ላይ የሚስተዋለው የሀይል መቆራረጥ እንደሚቀንስም ጠቀመው፤ ለዚህም አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና አካላት አመስግነዋል።

የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አመተሩፍ ሁሴን በበኩላቸው፥ በዞኑ ያሉ ጸጋዎችን መነሻ በማድረግ የባለሀብቱ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

በዞኑ 396 ኢንቨስትመንቶች በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ፍቃድ ወስደው እየሰሩ መሆኑን ያነሱት ኃላፊዋ ከነዚህ ውስጥ ከ120 በላይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች መሆናቸውም አመላክተዋል።

በዞኑ የማንፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ዘርፍ በሙሉ አቅም ማምረት እንዳይችሉ የሀይል አቅርቦት እጥረት ይስተዋል እንደነበር ጠቅሰው፤ መምሪያው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንም አመላክተዋል።

መምሪያው ማንፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመሆን የኢንደስትሪ ማዕከሉ ራሱን የቻለ የሀይል አቅርቦት እንዲያገኝ 32 ኪሎሜትር የመስመር ዝርጋታ መደረጉን አውስተው ይህንንም በገንዘብ ሲተመን ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ተናግረዋል።

ይህም የኢንደስትሪ ማዕከላት አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት እንዲያገኙ እንደሚያደርግም አንስተው፤ ለዚህም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና አካላት አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ሀይል የመካከለኛ ሶስት ሪጅን ዳይሬክተር አቶ እስማኤል ሙዘይን ለኢንደስትሪ ማዕከላት ራሱን የቻለ መስመር መዘጋጀቱን ጠቅሰው ይህም ኢንደስትሪዎች ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ ተጨማሪ ኢንደስትሪዎችን ወደ ዞኑ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ያስችላል ብለዋል።

የሀይል መስመር ዝርጋታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የኃይል መቆጣጠሪያ ብሬከር የመግጠም ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *