በዞኑ በተቀናጀ ግብርና ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የግብርናን ሽግግር እውን ለማድረግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የምናደርገው ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው ሲሉ አቶ አበራ ገልፀዋል።
ሀምሌ 15/2018(ወልቂጤ)
በጉራጌ ዞን በዘንድሮ የመኸር ወቅት በአዝርትና በሆሊታክልቸር 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የጉራጌ ዞንና የአበሽጌ ወረዳ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በወረዳው እየተሰሩ ባሉ የግብርና ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት በጉራጌ ዞን እየተሰሩ ያሉ የግብርና ስራዎች የምግብ ሉአላዊነታችን ለማረጋገጥ የምናደርገው ስኬታማ ጉዞ ማሳያ ሲሆኑ አበሽጌ ወረዳ ደግሞ አንዱ ነው።
በዞኑ የሌማት ትሩፋትና የተቀናጀ ግብርና ስራ በአርሶ አደር ጓሮ ተግባራዊ በማድረግ የቤተሰብ ብልጽግናውን ያረጋገጠ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስታውቀዋል።


በዘንድሮ በኸር ወቅት 177 ሺ 800 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 10 ነጥብ 5 ኩንታል ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጉራጌ ዞን 46 ሺ ሄክታር መሬት በበቆሎ የተሸፈነ ሲሆን አበሽጌ ወረዳ ሰፊውን ድርሻ ይወስዳል ነው ያሉት።
አቶ አበራ አክለውም መንግስትና አርሶ አደሩ የአየር ሁኔታውና የነዳጅ እጥረቱ ሳይበግረው ለግብርናው ልዩ አጽንኦት በመስጠቱ ዛሬ ላይ የተሻለ ምርት ማየት እየተቻለ መሆኑን አስታውቋል።
በርካታ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ከብቶች፣ ዶሮ፣ ቅመማ ቅመም፣አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡናና እንሰት በስፋት በማምረት ድህነትን አሸንፈው ሀብት መፍጠር ችለዋል።
በዚህም በአበሽጌ ወረዳ በተቀናጀ ግብርናና በክላስተር እርሻ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ሥራዎች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የምናደርገው ስኬታማ ጉዞ ማሳያ ናቸው ብለዋል አቶ አበራ።
የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በዞኑ ከዚህ በፊት ታርሰው የማይታወቁ መሬቶች በስፋት በማረስ ፣ምርታማነት በመጨመር ፣ግብርና ለአርሶ አደሩ ምግብን በራስ ከመቻል አልፎ የገቢ ምንጭ እየሆነው ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም በአበሽጌ ወረዳ እየታየ ያለው አመርቂ የግብርና ስራ እጅግ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ገልጸው ለዚህ ደግሞ ግብአት በወቅቱ እንዲቀርብ፣በቂ ነዳጅ እንዲኖር፣የኬሚካልና ሌሎች የአረም ቁጥጥሮች በመደረጋቸው ጥሩ ምርት እንዲታይ አስችሏል ነው ያሉት።
አቶ ደሳለኝ አክለውም በመንግስት የሚወርዱ ኢኒሼቲቮች ተግባራዊ መደረጋቸው ጠቁመው ለአብነትም የሌማት ትሩፋትና የተቀናጀ ግብርና በዞኑ ውጤት አስገኝቷል ሲሉ ጠቅሰዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጅኋር በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎች በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል ብለዋል።
በመሆኑም በወረዳው የቡና፣ የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶች ከተበታተነ አመራረት ወጥተው ወደ ክላስተር ስርዓት በመሸጋገራቸው ምርታማነትና የገበያ ተወዳዳሪነት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
አበሽጌ ወረዳ በምርታማነት፣ በክላስተር እርሻ፣ በመስኖ ልማት፣ በተቀናጀ ግብርናና በማህበረሰብ ተሳትፎ የተገኘው ለውጥ የዞኑና የክልሉ የግብርና አቅም በተግባር እየተገለጸ ነው ብለዋል አቶ ካሱ።
በቆሎ የአበሽጌ ወረዳ መገለጫ ነው ያሉት አቶ ካሱ በዘንድሮ አመት 38 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በበቆሎ ክላስተርና በሜጋ ክላስተር መሸፈኑ አብራርተዋል።
የአበሽጌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድል ከሪም ናስር በበኩላቸው የወረዳው ምቹ የአየርና የአፈር ጸጋ እንደ እድል በመጠቀም ሁሉም እንደ አቅሙ ግብርናን በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በወረዳው ቅመማ ቅመም ፣ጤፍ ፣ቦቆሎ ፣ቦለቄ ፣ሽምብራ ፣እንሰት፣ቡናና የፍራፍሬ ምርቶች በስፋት እየተመረቱ ነው ብለዋል አቶ አብድልከሪም።

6ቱ የግብርና ምሰሶዎችን ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን በተለይ ወደ ውጭ የሚላኩ የቡና፣ የቦለቄ እና የኮረሪማ ምርት ላይ በአጽንኦት እየተሰራ መሆኑ ተናግረዋል።
በበቆሎ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱ አመላክተው 4ሺ 800 ሄክታር መሬት በጤፍ ለመሸፈን መታቀዱ አብራርተዋል አቶ አብድልከሪም።
ወጣት ነጻነት በለጠ በአበሽጌ ወረዳ ከቅጥር ስራ ወጥታ በዶሮ እርባታ ተሰማርታ ሀብት መፍጠር መቻሏ ተናግራለች።
ወጣቶች በግብርና ልማት ቢሰማሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ልምዷን አካፍላለች ወጧቷ።
አርሶ አደር አቶ ሀይሉ ዴሲሳ በቆሎ በስፋት እያመረቱ መሆኑን ገልጸው በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አስታውቀው ግብርናው ድህነትን አሸንፈውበት ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ እንደሆናቸው አስገንዝበዋል።
