የጉራጌ ብሔርን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግ አበረታች ተግባራት ማከናወን ተችሏል ሲሉ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ ገለፁ

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የጉራጌ ብሔርን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግ አበረታች ተግባራት ማከናወን ተችሏል ሲሉ /ሮ መሰረት አመርጋ ገለፁ።
ነሀሴ 09/2018 (ወልቂጤ)
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የጉራጌ ብሔርን ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ለማሳደግ እንዲሁም ቅርሶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ አበረታች ተግባራት አከናውኗል።

የመምሪያው ኃላፊ ወ /ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት አመት የጉራጌ ብሔር ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ ለማሳደግ አበረታች ተግባራት ማከናወን ተችሏል።
የጉራጌ ማህበረሰብ በርካታ ባህላዊ እሴቶች እና ቅርሶች ያሉት ሲሆን እነዚህ ሀብቶች ለይቶ በማደራጀት ከአካባቢ አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።


የመስቀልና የአረፋ በዓላት ባህላዊና ኃይማኖታዊ ይዘታቸው እንደተጠበቀ የክልል፣ የሁለቱ ዞኖች፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ፣ የጉልባማ፣ የወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በአደባባይ በድምቀት ማክበር ተችሏል።
በዓላቱ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘታቸው እንደተጠበቀ ከማክበር በተጨማሪ በርካታ ባህላዊ ቁሳቁሶች፣ ባህላዊ ምግቦችና አልባሳት ለኤግዚቢሽን በማቅረብ ማስተዋወቅ መቻሉን አስረድተዋል።
የልጃገረዶች ቀን “ነቆ/ረቆ” በዞኑ በሚገኙ በሁሉም መዋቅሮች ት/ቤቶች፣ በገበያና በጀፎረ ላይ በድምቀት እንዲያከብሩ ተደርጓል።


የጉራጌ ማህበረሰብ የእናቶች ቀንን የማክበር የዳበረ ልምድ እንዳለው ገለፁት ኃላፊዋ የዘንድሮ ዞናዊ የእናቶች ቀንን “አንትሮሽትን”በወርሀ ጥር በአበሽጌ ወረዳ ማክበር ተችሏል ብለዋል።
በበጀት አመቱ ክትፎና ጀፎረ ከአካባቢ አልፎ የአለም አቀፍ ቅርስ ለማድረግ በርካታ የማስታወቂያ ተግባራት ተከናውነዋል።


ክትፎን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከኢፌድሪ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር የተካሄደው ጥናትና ምርምር በባለድርሻ አካላት ተገምግሞ፣ አስፈላጊ አስተያየቶች ከተካተቱበት በኋላ እርክክብ ተደርጓል።
የጉራጌ ጀፎረ እንደ ሀገር የብዙሀኑን ቀልብ የሳበ ድንቅ ቅርስ በመሆኑ ሀብቱ ይበልጥ ለማስተዋወቅ መንግስት የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጀፎረን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ሙህራን እንደ ዶ/ር መስፍን ሳህሌ፣ ዶ/ር አብነት ሽፈራ ያሉትን ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራዎች በማከናወን ግኝቱ ለዞኑ ማስረከባቸውን አስረድተዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያላቸው ጀፎረዎች ማልማት የተቻለ ሲሆን ለ40 ጀፎረዎች የይዞታ ማረጋገጫ ደነድ ተሰርቶላቸዋል።


ይህ ደግሞ ጀፎረ ይበልጥ እንዲጠበቅ ዘመን ተሻጋሪነቱን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
የባህላዊ ምግቦች፣ መድሀኒቶች፣ የወጌሻ ስርዓት እና የሌሎች የባህል ውጤቶች መረጃ ተሰብስቦ በማደራጀት መሰነድ መቻሉን ገልፀዋል።
ጉራጊኛ የስራ፣ የትምህርትና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን በዞኑ ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ከነሀሴ 2/2017 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
የተቋማት አቅጣጫ እና ስማቸውን የሚገልጽ ታፔላ በጉራጊኛ ለመፃፍ ከተለያዩ ዘዬዎች ገላጭ የሆኑ ቃላት የማሰባሰብ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።
በተጨማሪም በት/ቤቶችና የመበመንግስት መስሪያ ቤቶች ሳምንታዊ የጉራጊኛ ቀን በማወጅ እየተተገበረ ሲሆን ተረት ተረት፣ እንቆቅልሾችና ሌሎችም በጉራጊኛ ተዘጋጅተው ማደራጀት ተችሏል።

ወደ ዞኑ የሚገቡ የቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚገኝ ሲሆን በበጀት አመቱ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ዞኑን የጎበኙ ሲሆን ከእነዚህም ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑት የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንደነበሩ ኃላፊዋ ገልፀዋል።
በዞኑ የ171 ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህባት መረጃ በዝርዝር ተሰብስቦ የተደራጀ ሲሆን ሀብቶቹ ለማስተዋወቅ በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
በዞኑ የሚገኙ ቀልጣፋና ጥራት ያላቸው አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችና ሎጆች ቁጥር እያደገ መሆኑንም አውስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *